129ኛው የአድዋል ድል መታሰቢያ በዓል እና ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በዛሬው እለት በበርሊን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ኤምባሲ በደማቅ ዝግጅት ተከብሯል፡፡ በአከባበር ስነስርአቱ ላይ ተጋባዥ ኢትዮጵያዊያን፣ ትውልድ ኢትዮጵያዊያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች የተገኙ ሲሆን በዓላቱን የሚዘክር አጭር ፊልም እና የሙዚቃ ስራዎች ቀርበዋል፡፡
በፕሮግራሙ ላይ ንግግር ያደረጉት አምባሳደር እስክንድር ይርጋ የአድዋ ድል ከኢትዮጵያ እና አፍሪካ አህጉር ባለፈ የጥቁር ህዝቦች ሁሉ ደማቅ ድል መሆኑን በማውሳት፣ በዓሉን በኩራት ከማክበር በተጓዳኝ የአድዋን ድል ገድል በሁሉም ዘርፎች ዛሬም ለመድገም ከእኛ ትውልድ ምን ይጠበቃል የሚለውን መሰረታዊ ጥያቄ በመመለስ ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡ የዘመናችን አድዋ የሆነው ታላቁ የህዳሴ ግድብ እንዲጠናቀቅ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን፣ ትውልድ ኢትዮጵያዊያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች የበኩላቸውን አሻራ እንዲያስቀምጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በዓሉ ከዓለምአቀፉ የሴቶች ቀን ጋር በጋራ መከበሩ በድሉ ወቅት እናቶቻችን የተጫወቱትን አይተኬ ሚና ለመዘከር፣ ያለ ሴቶች ተሳትፎ የሚሳካ ሙሉ ድል እንደሌለ ለመዘከር ልዩ አጋጣሚ እንደፈጠረ ተናግረዋል፡፡
በዝግጅቱ ላይ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ሴቶች ማሕበር ሊቀመንበር መልእክት ያስተላለፉ ሲሆን ተጋባዥ እንግዶች በአድዋ ድል፣ የሴቶች ተሳትፎ እና የኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ያተኮሩ አስተያየቶችን ሰጥተዋል፡፡




