ከኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት የተውጣጣ የልዑካን ቡድን በጀርመን ከተሞች በበርሊን፣ ሙኒክ ፣ በኑረንበርግ ፣ በፍራንክፈርት ፣ በስቱትጋርት እና በኮለን ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን አደረጃጀቶች ጋር ሐምሌ 05 ቀን 2015 ዓ.ም. ባደረጉት ውይይት ከሀገራቸው ጋር ያላቸውን ትስስር አጠናክረዉ እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

የልዑካኑ ቡድኑ ከጁላይ 05 እስከ 11, 2023 በኤምባሲያችን በአካል በመገኘት የአዉትሪች እና ኢንስፔክሽን ስራዎች ያከናወኑ ሲሆን በቆይታቸዉም ኤምባሲያችን ከሚሸፍናቸዉ ከተሞች ከሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትዉልደ ኢትዮጵያውያን የዳያስፖራ አደረጃጀቶች ጋር ዉይይት አድርጓል።
በዉይይት መድረኮቹ የተሣተፋት በሙኒክ ፣ በኑረንበርግ ፣ በፍራንክፈርት ፣ በስቱትጋርት እና በኮለን የሚገኙ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ፣ በየሀገራቱ ከሚገኙ የተለያዩ የኮሚኒቲ አመራሮች፣ ታዋቂ ግልሰቦች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ የወጣት ማህበራት እንዲሁም ከምሁራንና የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ጋር የዳያስፖራውን ተሳትፎና ተጠቃሚነት አጠናክሮ ማስቀጠል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ምክክር አድርጓል።

በፍራንክፈርት በነበረዉ መድረክ በጀርመን የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክሪሲያዊ ሪፐብሊክ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደርና ልዩ መልእክተኛ ክብር አምባሳደር ፍቃዱ በየነ የኮሚኒቲው አደረጃጀት አገራችን በምትፈልጋቸዉ ሁሉ ኢትዮጵያውያንን እና ትዉልደ ኢትዮጵያዉያንን በማስተባበር አገራቸውንና ሕዝባቸዉን ሲያገለግሉ መቆየታቸዉን በማስታወስ አደራጃጀቶቹ ዛሬም አገራዊ ትስስራቸዉን አጠናክረው ለመቀጠል በመሰባሰባቸዉ ምስጋና አቅርበዋል።

በመድረኮቹ ላይ ዳያስፖራው ከሀገሩ ጋር ያለውን ትስስር ለማሳደግ የተዘጋጁ ስልቶችና የዳያስፖራ ተሳትፎን ለማበረታታት በመንግስት የተዘረጉ ምቹ ሁኔታዎች ዙሪያ ከልዑካን ቡድኑ ማብራሪያ ተሰጥቶ ውይይት ተካሂዶባቸዋል፡፡

በመድረኩ ላይ ለተነሱ ጥያቄዎችም መረጃና ማብራሪያ የቀረበ ሲሆን፣ ከወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታ ጋር በተያያዘ በተሳታፊዎች በተነሱ ሀሳቦች ላይ ውይይት ተደርጓል።

ተሳታፊዎችም በአገራዊ ጉዳይ የጋራ መግባባት ለመፍጠር እንደዚህ ያሉ መድረኮች ፋይዳቸዉ የጎላ መሆኑን በማንሳት በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ አዎንታዊ ሚናችንን አጠናክረው በመቀጠል በሀገራዊ የልማት ጥሪዎች ላይ ያላቸውን ተሳትፎ ለማሳደግና የትውልድ ሀገራቸውን ገጽታ ለማስተዋወቅ እንደሚሰሩ ገልጸዋል ።

Disclaimer: The official text of the Embassy Website is the English language version. Any discrepancies or differences created in translations are not binding and have no legal effect for compliance or enforcement purposes.

X
Twitter
Facebook