(ሰኔ 12 ቀን 2015ዓ.ም ) በበዓሉ ላይ የተገኙት የጀርመን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ምክትል ሚሲዮን መሪ አምባሳደር ሃይላይ ብርሃነ ቤተክርስቲያኒቷ በ40 ዓመት ጉዞዋ በጀርመን ሀገር የኢትዮጵያውያንን አንድነት በማጽናት ላደረገችው አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል ።
በዓሉ ብፁዕ አቡነ አብርሃም የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅና የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤ የብፁዕ አቡነ ዲዮናስዮስ የጀርመንና አካባቢው እና የምሥራቅ ጎጃም ሊቀ ጳጳስ፤ መልአከ መዊዕ ልሳነ ወርቅ ውቤ የጀርመንና አካባቢው ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ፣ ክቡር አምባሳደር ሃይላይ ብርሃነ ተሰማ በጀርመን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ምክትል ሚሲዮን መሪ የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት አስተዳዳሪዎች፣ ካህናት፣ መዘምራን እና ምእመናን በተገኙበት እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ወዳጆች በተገኙበት በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል ።
ክቡር አምባሳደሩም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በጀርመን ሀገር በ40ዓመት ሐዋርያዊ ተልእኮ በጀርመን እና አከባቢው የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ-ኢትዮጵያውያ አንድነት በማጠናከር እንዲሁም እንዲሁም ምዕመናንን በማስተባበር ስታደርግ ለቆየችዉ ሀገራዊ ድጋፍ ፣ በፐብሊክ ዲፕሎማሲ ረገድ ከጀርመን ሀገር ጋር ያለንን ግንኙነት እንዲጠናከር ላደረጉት አስተዋጽኦ በኤምባሲያችን ስም ከፍ ያለ ምስጋና አቅርበዋል ።
እንዲሁም በመጠናቀቅ ላይ ለሚገኘው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እና ገበታ ለትውልድ ሀገራዊ ልማት ቤተክርስቲያኒቷ ምእመናን በማስተባበር ስታደርግ የቆየችውን ድጋፍ አጠናክራ እንድትቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።