የካቲት 23 ቀን 2015 ዓ.ም. በኤምባሲያችን የዓድዋ ድል በዓል ተከብሯል፡፡ በእለቱም ክቡር አምባሳደር ተፈሪ ታደሰ፣ በበርሊን የኢትዮጵያ ፌ.ዲ.ሪ ኤምባሲ ምከትል የሚሲዮን መሪና ጉዳይ ፈጻሚ እንኳን ለ127ኛው የዓድዋ ድል በዓል አደረሳችሁ በማለት ንግግራቸውን የጀመሩ ሲሆን፣ በመቀጠልም አድዋ አያቶቻችን ከደቡብ እሰከ ሰሜን፣ ከምሥራቅ እሰከምእራብ በአንድነት ተሰባስበው ድል የተቀዳጁበት መሆኑንና አገራችን ኢትዮጵያን ደማቸውን አፍስሰው አጥንታቸውን ከስክሰው ያቆዩን መሆኑን፣የአስተሳሰብ ልእልናችንን ያሳየንበት፣ በቅኝ አገዛዝ ሥር የወደቁ ለትግል መነሻ ያደረጉበት ጭምር እንደሆነ አንስተዋል፡፡ ስለዚህም የአድዋ ድል የአለም ታሪክን የለወጠ መሆኑን በማንሳት ቀጥሎም ከኤምባሲው ሠራተኞች ጋር በዓሉን አስመልክቶ ውይይት ተደርጓል፡፡ በውይይቱም አድዋ ከዲፕሎማሲ ሥራችን ጋር ግንኙነት ያለው መሆኑን ለአብነት ያክል የውጫሌ ውልን በማንሳት እንዲሁም አድዋ የፓን አፍሪካኒዝም መነሻ መሆኑንና ከአድዋ በመነሳት ያሉብንን ችግሮች በኛ ዘመን የምንሻገርበት ማድረግ እንደሚገባ ተንጸባርቋል፡፡

ቀጥሎም ማምሻውን በበርሊን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ኤምባሲ በተወከልንባቸው አገሮች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልድ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች በተገኙበት በዙም የዓድዋ በዓል ተከብሯል፡፡ በዚህ ፕሮግራም ላይም ክቡር አምባሳደር ተፈሪ ታደሰ የሚሲዮኑ ምክትል መሪና ጉዳይ ፈጻሚ በእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት በዓሉን የከፈቱ ሲሆን፣ ለ127 ጊዜ የሚከበረውን የአድዋ በዓል “ለአገራዊ አንድነት፣ ጀግንነት እና ጽናት መልህቅ” በሚል መርህ በጋራ ለማክበር በመቻላችን ትልቅ ክብር ይሰማናል ሲሉ ገልጸዋል፡፡ ለአድዋ ድል ላበቁን አያቶቻችን ክብርና የድሉን ቀን የምናከብርበት አንድ ሆነን ሁላችንም በእኩልነት ለአገራችን የምንሰራበት ቁርጠኛ ሆነን የምንቆምበት እንዲሁም መስዋእትነት ለመክፈል ትምህርት የምንወስድበት መሆኑን በመግለጽ፣ ኢትዮጵያውያን እጅ ለእጅ ተያይዘን ወደ ላቀ አስተሳሰብና አመለካከት በአንድነት መሻገር ይገባናል ሲሉም አሰምረውበታል፡፡

በእለቱም ክብርት አምባሳደር ሙሉ ሰለሞን በክብር እንግድነት በመገኘት በዓሉን አስመልክቶ ገለጻ የሰጡ ሲሆን፣ቀስቃሽ ግጥምና ፎከራዎችን አሰምተዋል፣ ከታዳሚዎች ጥያቄና አስተያየት ቀርቦ መልስ የተሰጠበት ሲሆን፣ የእለቱን ፕሮግራም ክቡር አምሳሳደር ተፈሪ ታደሰ ማጠቃለያ በመስጠት የበዓሉ ፍጻሜ ሆኗል፡፡

 

 

Disclaimer: The official text of the Embassy Website is the English language version. Any discrepancies or differences created in translations are not binding and have no legal effect for compliance or enforcement purposes.

X
Twitter
Facebook