ክቡር አምባሳደር ፍቃዱ በየነ በጀርመን ከኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ኤምባሲ ጋር አብረው ከሚሰሩት በጀርመን ከብሬመን፣ ከሐምቡርግ፣ ከሙኒክ እንዲሁም በሰሎቫክ ሪፐብሊክ ከሚገኙት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. የክብር ቆንስሎች ጋር የትውውቅ ስብሰባ አድርገዋል።
በመድረኩም ክቡር አምባሳደሩ የ6 ወራት የመንግስት አፈጻጸም ዋና ዋና ስኬቶችና ተግዳሮቶችን ለተሳታፊዎቹ ያጋሩ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ ኖቬምበር 02/2022 የተፈረመውን የሰላም ስምምነትና የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግንበታ አስመልክቶ የሀገራችንን ወቅታዊ ሁኔታ በመዳሰስ እንዲሁም ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች እየሰራች ያለችውንና ያሉትን እድሎች ለክቡራን ቆንስሎች አስረድተዋል።
ክቡር አምባሳደሩ በቅርቡ በኢትዮጵያ Invest Ethiopia በሚል በሚካሄደው ታላቅ የኢንቨስትመንት ኩነት የክብር ቆንስሎቹ እያደረጉ ላሉት አስተዋፅኦ በማመስገን የክቡር ቆንስሎቹ በአሁኑ ሰዓት እያደረጉ ያሉትን የነቃ ተሳትፎ አጠናክረው እንዲቀጥሉና በዚህም የኤምባሲውን ያልተገደበ ድጋፍ እንደሚያገኙ ቃል ገብተውላቸዋል።
የክብር ቆንስሎቹ በበኩላቸው ክቡር አምባሳደሩ ተሹመው ወደ ጀርመን ሀገር በመምጣታቸው የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት አስተላልፈው ከኤምባሲው ጋር ያላቸውን የጠበቀ የሥራ ግንኙነት የበለጠ በማጠናከር አብሮ ለመሥራት ያለቸውን ፍላጎት ገልጸዋል።
ክቡር አምባሳደሩ ከተሳታፊዎች ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተው በቀጣይም ተመሳሳይ መድረኮችን እንደሚያመቻቹ ቃል ገብተዋል፡፡